ከቡናችን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ ለመሆን
December 4, 2021
በዓለም-አቀፍ ደረጃ ቡና ተፈላጊነቱ እየጎለበተ መጥቶ ነዳጅን ተከትሎ 2ኛው ሰፊ ገበያ ያለው ምርት ነው፡፡
በኢትዮጵያ 30 ሚሊየን የሚገመት ህዝብ የዕለት ኑሮው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቡና ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከዓመታዊ ጥቅል ምርቷ ከ5 በመቶ የሚበልጠው ድርሻ በቡና የተያዘ ነው፤ 25 ከመቶ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪ የሚገኘውም ከዚሁ አርሶ አደር ማሳ ተለቅሞ ለውጭ ገበያ ከሚቀርብ ቡና ነው፡፡
አገራችን ቡናን ለዓለም ገበያ አስተዋውቃ አርሶ አደሮቿም ተፈጥሮአዊ/ኦርጋኒክ/ እና ልዩ ልዩ ተወዳጅ ጣዕም ያላቸውን የአረቢካ ቡና ዓይነቶች ለዓለም ብታበረክትም ተጠቃሚነቷ ከብራዚል፣ ኮሎምቢያና ቬትናም አኳያ ሲነጻፀር ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የሐገራችን የቡና ምርታማነት በአማካይ በሄክታር ከ7 ኩዊንታል የማይበልጥ ሲሆን በንጽጽር ብራዚል፣ ኮሎምቢያና ቬትናም ደግሞ በሄክታር ከ3 እና 4 እጥፍ በላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ምርታማ የሆኑና በሽታን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በምርምር የማፍለቅና የማዳረስ አቅም አናሳ በመሆኑ በቀጣይ በላቀ ትኩረት መስራትን ይጠይቃል፡፡
የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ከችግኝ ጣቢያ ጀምሮ እስከ ቡና ለቀማና መላክ ድረስ ያለው የቡና አያያዝ /Agronomic Practices/ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡
የቅጠል ቡና/ haytta tukkiya/ ለማፍላት ተብሎ አረንጓዴውን የቡና ቅጠል መሸምጠጥ የቡና ግንድ ተገቢ ምርት እንዳይሰጥ ስለሚያደርግ በስሎ ከቡናው ቅርንጫፍ የተራገፈውን ቢጫ የቡና ቅጠል/Aara tukkiya haytta/ ብቻ ለቅሞ ለማፍላት መጠቀም ይቻላል፡፡
አሀን ላይ ኦርጋኒክ የሚለው ሀሳብ በአምራቹና በባለሙያው መካከል ብዥታ ያለበት ነው፤ እሱን ማጥራት ያስፈልጋል፡፡
ማዳበሪያ የምርታማነትን መጠን እንደሚጨምር የአደባባይ ምስጢር ነው፤ እናም በምናመርተው ቡና ላይ የተመጠነ ማዳበሪያ በመጨመር ቡናው ጤንነቱን ጠብቆ እንዲመረት ቢደረግ የምርቱ ተፈላጊነት በዓለም ገበያ ፈላጊ አላገኘም/አያገኝም/ የሚል ግብረ-መልስ ከሸማቹ እንዳልተሰጠ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቡና ማሳ ለማስፋት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡
የተሻለ ጥራት ያለው / የበሰለ ቀይ እሸት / ቡና አምርተን የተሻለ ዋጋ ለማግኘት የመደራደር አቅምን ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡
ቡናን በሽምጠጣ በመልቀም ሂደት, qoshiya,shoolluwaa, qawu’iya / ያልደረሰውን/ጭምር የመሰብሰብ ዕድል ስለሚፈጠር በቡናው ጥራት ላይ ከሚያሳድረው ተጽእኖ በተጓዳኝ በቡናው ቅርንጫፍ ደህንነት ላይም ጉዳት ሊያስከትል ይችላል::
የቡና ፍሬ ለባዕድ ጠረን እንዳይጋለጥና እንዳያምቅ የማድረቂያውን፣ የማከማቻውን፣ የማጓጓዣ ትራንስፖርትና ተያያዥ ማደረጃ ስፍራዎችን ንጽህና መጠበቅ ለጥራቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
በተበጣጠሰ ማሳ ላይ ለሚያመርቱ አርሶ አደሮች የሚደረገው ሙያዊ እገዛ እና የኤክስቴንሽን ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
የተራዘመና የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለቶችና ኮንትራባንድ በአምራቹ ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ጫና ስለሚያሳርፍ ሂደቱን ለማሳጠር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
ቡና ላይ እሴት ጨምሮ /በስርአቱ ተቆልቶ፣ተፈጭቶና ታሽጎ ወደ አውሮፓና አሜሪካ አገሮች መላክ/ በጥሬው ከመላክ አስር እጥፍ የሚደርስ ጭማሪ እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡


